እንደ
ወያኔ/ኢህአዴግዊ ሀገርንና ትውልድን የሚያጠፋ እኩይ አመለካከትና ምግባር ይዞ ተነስቶና ተሳክቶለትም የሚገዛ
ከኢትዮጵያ ውጭ በዓለም ላይ ያለ ሀገር የለም። የሚገዛ ህዝብም የለም። እንደ ወያኔ/ኢህአዴግ የገዛ ወገኑንና
ሀገሩን በጠላትነት ፈርጆ፣ ታጥቆና ተደራጅቶ የሚወጋና የሚያፈራርስ የለም። እንደ ወያኔ/ኢህአዴግዊ አገዛዝም
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊንን የማጥፋቱንና የመበታተኑን ምግባር እንዲያቆም እሽሩሩ የተባለና እየተለመነ ያለ የለም።
...
በልመና ቢሆን ...
ፍትህ - እኩልነት
በልመና ቢሆን ...
ነፃነት - አንድነት
በልመና ቢሆን ...
ሠላምና ሕይወት፤
እመጣ ነበረ - አንች ካለሽበት
ትመጭልኝ ነበር - እኔ ካለሁበት
ዓለም ይሆን ነበር፣ የሁላችንም ቤት።
እንደ
ደርግ ያለ አምባገነን መንግሥት ሀገሩን በክህደትና በጥላቻ ለተሞሉ፤ እንደ ሻዕቢያዊንና እንደ ወያኔያዊያን ላሉ
ሀገሩን አሳልፎ የሰጠ የለም። እንደ ወያኔ/ኢህአዴግ ያሉ ተቃዋሚዎች ልፍስፍስ፣ ወኔ ቢስ፣ እርስ-በርስ የሚናቆሩና
ከትላንቱ የማይማሩ፣ ሁሌም የጠላት መሳሪያ ሆነው የሚያገለግሉ “ቦለቲከኞች” ማግኘት ይከብዳል።
አንድ
ጀርመናዊ የጥንት ፈላስፋ “መግደልም ሆነ መገደል በፍጹም አልፈልግም፤ ግን ክብሬ ከሚዋረድ ከሁለቱ አንዱን
እመርጣለሁ።” ማለቱ ይነገራል። እኛ ኢትዮጵያዊያን ግን ሳንታገልም፣ ሳንኖርም፣ የቁም ሞትንና የውርደት ሕይወትን
“መኖር” ብለነው፤ ኢትዮጵያን የሚያክል ሀገር በሀገር ሻጭ ልጆች፣ የልጅ ልጆቻቸውና በሆድ-አደር ሎሌዎች
ስትፈራርስና አንጡራ ሀብቷ የባዕዳንና የወያኔዎች መቀለጃ ሲሆን እያየን ዓመታት አሳለፍን። ግፋ ቢል እነሱ ሥራቸውን
ሲሰሩ እኛ እናወራላቸዋለን። እጅግ በጣም ጥቂት በጣት የሚቆጠሩት እውነተኛ ሀገራዊ ትግል ቢጀምሩም፤ በግፈኛ
ወያኔዎች የሚደርስባቸው ግድያና እስራት አንሷቸው፤ አኛ የተለያየ ስም እንሰጣቸዋለን።
በዚህ
በያዝነው ዘመን፣ ሰው “ሰው" በመሆኑ ብቻ ተከባብሮና ተሳስቦ፤ ድንበር እያፈረሰ በአብሮነት መኖርና መበልጸግ
በተቻለበት ዓለም፤ በኢትዮጵያ ግን ለእውነትኛ ሀገራዊ ልዕልና፣ ለህዝቦቿ አንድነትና ህልውና የሚቆም መጥፋቱ
ሲታሰብ፤ የምናሳዝንና የሚታዘንልም ዜጎች ብቻ ሳንሆን፤ በእርግጥም ጤንነታችንም የሚያጠያይቅ ሆኗል። ለዚህም ነው
አቶ ገሪማ መታፈሪያ የሚከተለውን ስንኝ የቋጠሩት። …
“... ሁሉ በሽተኛ፣ ሁሉ ራሴን ባይ
ባገሬ ደህና ሰው ላይገኝ ነወይ?
ባገሬ ጤነኛ ላይገኝ ነወይ? ..."
በአጠቃላይ በስብዕናችን፣ በመፈሳዊነታችን፣ በማንነታችን፣ በኢትዮጵያዊነታችን፣ ... ወርደን ... ወርደን ... ወርደን ...
-
በዓለም የመጨረሻዋ ደሃ፣ ተመጽዋችና ስደተኛ ህዝቦች መሆናችን አልበቃ ብሎ፤ አንድ ቁጥር ዘረኛና አምባገነን
ሥርዓት የምናስተናግድና “ኢትዮጵያዊ አይደለንም እያሉን” የምንገዛላቸው እኛ ኢትዮጵያዊያን ነን።
-
ገዥዎቹ ወያኔዎችና ሆድ-አደር ሎሌዎቻቸው በዓለም ላይ አንድ ቁጥር የደሃ-ደሃ የሆነች ሀገር እየገዙ፤ ባለጸጋ
ሀገሮች እንኳ' ሊያልሙት የማይችሉትን የተንደላቀቀና የተፈላሰሰ፤ ግን የአውሬነት ኑሮ የሚኖሩባት ሀገር ኢትዮጵያችን
ነች።
-
ፊደል ቆጥረናልና ተምረናል የሚሉት የሀገሪቱ ዜጎች፤ ያስተማራቸውን ህዝብ ከድህነትና ከድንቁርና አውጥቶ፣ ፍትህና
እኩልነት ያለበት ሀገር ለመገንባት በመታገል ፈንታ፤ ከእነ'ሱ በእውቀትም ሆነ በሰብዕና ለሚያንሱ የወያኔ ቡድኖች
ጉዳይ አስፈጻሚ በመሆን፣ ወገናቸውንና ሀገራቸውን ለሆዳቸው፣ በሆዳቸው የሚሸጡ ፍጡራን እንደ አሸን የሚፈላባት ሀገር
ኢትዮጵያ ነች።
-
ዜጋው መጠለያ ጎጆ የሚቀልስበት ቦታና ጥማድ በሬዎቹን የሚያውልበት ሽራፊ መሬት ተነፍጎት፤ የኢትዮጵያን ውድቀትና
ጥፋት እንደ ማለዳ ፀሐይ ለሚናፍቁ፤ ግን እየተለመኑ ሀገር እየተቆረሰ የሚታደልባት ሀገር ኢትዮጵያ ነች።
-
በተለይም ወጣቱ ትውልድ በአገዛዙና በሀገሪቱ ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ፤ የሚበጀውን ለራሱና ለወገኑ ከመታገል ይልቅ፤
ባዕዳንን ተስፋ በማድረግ፤ ለባህርና ለውቅያኖስ አሳ ነባሪ፣ እንዲሁም ለበርሀ አሸዋ 'ራሱን አሳልፎ በመስጠት
ትውልድ እየጠፋባት ያለች ሀገር ኢትዮጵያ ነች። በሕይወት የተረፈም ለግርድናና ለሽርሙጥና ሲዳረግ፤ በሞቱት ስደተኛ
ወገኖቹ የሚቀና ኢትዮጵያዊ ብቻ ነው።
-
የህክምና ባለሙያዎች፤ በማንኛውም መንገድ ይሁን የሰውን ልጅ ሕይወት የመርዳትና የማትረፍ ዓላማ አድርገው በደሀው
የገበሬ ገንዘብ እንዳልተማሩና ቃለ-መሀላ እንዳልፈጸሙ ሁሉ፤ ወገናቸው ህክምና ፍለጋ አግዳሚ ወንበር ላይ ተጋድሞ
እያቃሰተ እያዩት፤ ነገር ግን የኃይል መስጫ ምግብ (ግሉኮስ) መግዣ ለግዜው ሣንቲም ስሌለው ብቻ ሕይወቱ እንድታልፍ
“ፍርድ” የሚሰጡባት ሀገር ኢትዮጵያ ነች።
- የኃይማኖት አባቶች እጅግ በሚዘገንንና በማይታመን መልኩ በዘረኝነትና በአፍቅሮ ንዋይ ታውረው፤ ለገዥዎች ሎሌነት በማደር፤ እምነት የረከሰባትና የተናቀባት ሀገር ኢትዮጵያ ነች።
- የሀገሪቱ የኪነ-ጥበብ ሰዎች፤ ንፋስ ወደ ነፈሰበት እየነፈሱ፣ የገዥዎች አፍና እጅ በመሆን፤ ክቡሩ የህሊና ሙያ ለከርስና ለጥቅማጥቅም የሚቸበቸብባት ሀገር ኢትዮጵያ ነች።
- ወያኔዎች የዘሩት የዘረኝነት ዘር አፍርቶ፤ በአሁኑ ወቅት የአንድ ቤት ቤተሰብ አባላት እንኳ' የማይተማመኑበትና፤ ወንድም ወንድሙን ለጥቅም አሳልፎ የሚሰጥበት ሀገር ኢትዮጵያችን ነች።
-
ኢትዮጵያ ... ግፈኞች፣ ወንጀልኞች፣ አምባገነኖች፣ ከሀዲዎች፣ ሆድ-አደሮች፣ ውሸታሞች፣ ሌቦች፣ ሀገር ሻጮች፣
ሙሰኞች፣ ጠባብ መንደርተኞችና ህሊና ቢሶች በኩራት ደረታቸውን ነፍተው የሚጎርሩባትና እንደ ሜዳ አህያ የሚፏልሉባት፤
በተቃራኒው ለእውነት፣ ለፍትህ፣ ለህሊናቸው፣ ለሀገራቸው ልዕልናና ለህዝባቸው ፍትህና እኩልነት የሚታገሉና የሚደክሙ
አንገታቸውን ደፍተውና አቀርቅረው የሚሄዱባት ሀገር ኢትዮጵያችን ነች። ...
ግን ምነዋ ኢትዮጵያ …?
እንደ ይሁዳ ከዱ ልጆችሽ ሸፈጡ
እንደ ኤሳው ሆኑ ቡክርናቸውን ሸጡ
በመታመን ፈንታ ኑፋቄን መረጡ።
እንደ ባህር አሸዋ - እንደ ሰማይ ከዋከብት
ምነዋ ኢትዮጵያ ... በዛብሽ ጠላት? ...
ጥር 07/05/2005 ዓ.ም ......በአስፋፋው ተጻፈ።
No comments:
Post a Comment