ልዩ ልዩ ግጥሞች

 እኔ ጉልት ስውል ጉልት ይውላሉ
እኔ አሣ ሳሰግር አሣ ያሰግራሉ
እኔ ፍራሽ ሳድስ ፍራሽ ያድሳሉ
ብቻ አመድ ብሸጥም አመድ ይሸጣሉ
ይሄ ሁሉ ሆኖም
ምቅኞች አይደሉም
ሀበሾች ምቅኞች ብላችሁ አትበሉ
እኔ ዛፍ ስተክል መቼ ዛፍ ተከሉ 


ኑረዲን ኢሣ






 ድምጽ አልባ ፊደላት

ፀጉሩን አንጨብሮ ፂሙን አጎፍሮ
ጥግ ተቀምጦ ለሚታየኝ ወጣት
ሂድና ታዘዘው ስጠው አንድ ድራፍት
ቅዳለት ደብል ጂን ሃሳቡን ይርሳበት
በፂሙ መጎፈር በፀጉሩ መንጨብረር
ቁጥር ፈታ በሚል በግንባሩ መስመር
ይታየኛል ቃንቃ ይታየኛል ነገር
እዛም ከጨለማው ብቸኝነት ውጣት
ሲጋራዋን ይዛ ለቆመችው ወጣት
ሂድና ታዘዛት የሚጠጣ ስጣት
ምጋ በተፋችው በጭሶቹ መሃል
ሴትነት ሲበደል እህትነት ሲጣል
እናትነት ሲጎድል
ይታየኛል ቃንቃ ይታየኛል ፊደል።


ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን











 እውነት ለፈለገ....

ፀሀይ ስትገባ
ጥያቄ ይወጣል ፀሀይን ተክቶ
ልቤም እስከንጋት ያልፈዋል ተኝቶ
ግድ ነው በለሊት አዳፍኖ ማለፉ
እሳትን ባመድ ሆድ ጥያቄን በን'ቅልፉ
ከጎረምሶች ከንፈር ጪስ እየነጠቀ
ከኮረዶች ጡት ላይ ሽቶ እየሰረቀ
ነፋሱ ይዞራል
ግና በምላሹ ምስጢር መች ይነግራል
መስኮቴን ብከፍተው
በብርድ ልብሴ ላይ ኮከቦች ፈሰሱ
እውነትለፈለገ ውበት ነው ወይ መልሱ










ደመወዙን ቢጥል
አንስተው ጠጡበት
ባርኔጣውን ቢጥል
ወስደው ደመቁበት
ከዘራውን ቢጥል
ተመረኮዙበት
በሄደበት ሁሉ
እየተከተሉ
በጣለው ሲያጌጡ
በጣለው ሲያተርፉ
ራሱን ሲጥል ግን
አይተውት አለፉ

በውቀቱ ስዩም
(ካንድምታ ላይ የተወሰደ )




 ጠላቴን ስመርቅ

በስልጣን ከፍ ከፍ
በዝና ከፍ ከፍ
በሀብትም ከፍ ከፍ
ወደላይ ከፍ ከፍ
ከፍ ከፍ.... ከፍ ከፍ
ከዛ የወደቅህ ዕለት አጥንትህ እንዳይተርፍ::

ገጣሚ ታገል ሰይፉ






የፆምፍቅር~
አተኩሬ ሳይሽ
ከንፈርሽ ያምረኛል
ልስምሽ ሳስብ ግን
ፆሙ ትዝ ይለኛl
መንገድ እየሄድን
ክንዴ ሊያቅፍሽ ሽቶ
ሳያቅፍሽ ይቀራል
ትሽሽቱን ፈርቶ
ውዴ እንዳንሳሳት
ፆሙ እስኪወጣ
ወde እኔ አትምጪ
በቃ እኔም አልምጣ
በሞገስጋሻው


የሸዋ አባት ልጁን ለትግሬ ካልሰጠ

የሐረር ነጋዴ ወለጋ ካልሸጠ
ፍቅር ወዴት ወዴት ወዴት ዘመም ዘመም
ሀገርም አለችኝ ወገን የኔ ህመምስሩ እንዳይበጠስ መቃጠሪያው ደሙ
አረንጋዴ ቢጫ ቀይ ነው ቀለሙ
እኔን የራበኝ ፍቅር ነው.እጅጋየሁ ሽባባው























**የደፈጣ ውጊያ**
ፍቅር ለጀማሪው
የደፈጣ ውጊያ
ተፈቃሪ አስፈሪ
ፍቅሩም ታላቅ ፍልሚያ
ከዛም ተፈቃሪን
ዱካውን ማሳደድ
በገባበት መግባት
በሄደበት መሄድ
በቅርበት መከተል
ሲጠጋም መሸሸግ
አድፍጦ መጠበቅ
ፍቅራዊ ማፈግፈግ
የወዳጅ ወዳጅም
ሆይ ሆይ ባይ ጓደኞች
ከፊል ጋዜጠኞች
ዘጋቢ ተንታኞች
ከፊሉ አቀጣጣይ
የፍልሚያው ድምቀቶች
ቶማስ ወልዴ


"እህ" ብዬ ሰማሁት ዝምታሽን
ያን የአይን ቁዋንቁዋ የውስጥ ውስጥሽን
"እህ" አልኩ አዳምጬው በጥሞና
አይንሽ አወጋኝ ፍቅር ነውና
ዝምታሽ ምን ይሁን ቃል መሰሰትሽ
ነገ በኔ ተቀይሮ ፍቅሬ እንዳያመልጥሽ
ቂም ያረገዘ ልብ በንዴት ይወለዳል
ቀናት ተገፍተው ዝምታም ይጮሐል
"እህ" ልበልሽ ንገሪኝ የውስጥሽን
ማፍቀር ደግ ነው ስበሪው ዝምታሽን
እኔም አይና ፋር አይኔ ግን አሳባቂ
ገብቶሻልና ፍቅሬ ካፌ እንዳጠብቂ
ተላልፈን ሓላ እንዳይቆጨን አደራ ተጠንቀቂ
እ-ህል ቢያንቅሽ ዕንቀቱን ተቀበይ
ወ-ርዶ እስኪያርፍ "እህ" በይ
ድ-ንገት የመጣ ይሔን ስቅታ
ሻ-ል እስኪልሽ ይውጣ ባፍ ወለምታ
ለ-በጎ ነውና መሰበሩ ዝምታ
ሁ-ሌም አስቢው እንዳይገልሽ ዝም ያልሽው ለታ
*ከሻጊዝ አዶናይ*

3 comments:

  1. ግጥሞቹ በጣም ደስ ይላሉ ጥሩ ጥሩ ይርግጥም ምርጫ ነው በዚው ቀጥይበት

    ReplyDelete
  2. ጥንካሬ ባይኖር በህሊና ጉዞ መችይረዳኝ ነበር ግጥምህ ግጥም ሆኖ

    ReplyDelete